ሃሰኩራ ጹነናጋ
维=>ሐ | ይህ መጣጥፍ «የሳምንቱ ትርጉም» ነው። (የካቲት 20 ቀን 1998 ተመረጠ።) ችሎታ ካለዎት፣ ከሌሎቹ ቋንቋዎች መረጃ በትርጉም እንዲጨመር ይርዱ! |
ሃሰኩራ ሮኩኤሞን ጹነናጋ (支倉六右衛門常長, 1563–1614 ዓ.ም.) ጃፓናዊ ሳሙራይ (መኮንን) እና የሰንዳይ ዳይምዮ (ገዥ) የዳተ ማሳሙነ ሎሌ ነበሩ። ከ1605 ዓ.ም. እስከ 1612 ዓ.ም. ድረስ ወደ ሜክሲኮ፣ እስፓንያ፣ ፈረንሳይ እና ጣልያን አገሮች አምባሳደር ሆነው ይፋዊ ጉብኝት አደረጉ። ከማንም በፊት ወደ አሜሪካ አህጉር የተላኩት የጃፓን መንግሥት ልዩ ተወካይ እሳቸው ነበሩ። ከዚያ በላይ የርሳቸው ተልዕኮ በታሪክ መዝገብ የሚታወቀው መጀመርያው ጃፓናዊ-ፈረንሳያዊ ግንኙነት ሆኗል።
ስለ ልጅነታቸው ብዙ ባይታወቅም፣ በታይኮ (እንደራሴ) ሂደዮሺ በኮርያ ላይ በተደረገው ወረራ ጊዜ በ1584 እና በ1589 ዓ.ም. ዘመቻዎች ልምድ ያለው ሳሙራይ ሆነው እንደ ተሳተፉ ይታወቃል።
በ16ኛው ምዕተ ዓመት ከተካሄደው አንድሬስ ዴ ኡርዳኔታ ጉዞ ጀምረው እስፓንያውያን በፊሊፒንስ የያዙትን መሬት መሠረት አድርገው በሜክሲኮና በቻይና መካከል ፓሲፊክ ውቅያኖስን ይሻገሩ ነበር። በ1563 ዓ.ም. ማኒላ ለምሥራቅ እስያ ሁሉ መሠረታቸው ሆነላቸውና።
የስፓንያ መርከቦች አንዳንዴ በመውጅ ትይዘው በጃፓን ዳር ላይ ሲሰበሩ በዚህ አጋጣሚ ግንኙነት ከአገሩ መጣ። እስፓንያውያን የክርስትናን ሃይማኖት ወደ ጃፓን ለማስፋፋት ፈልገው ነበር። ነገር ግን ተፅእኖ ወደ ጃፓን ለመዘርጋት የተደረገው ጥረት ከ"ኢየሱሳውያን" ወገን ብርቱ ተቃውሞ አገኘ፤ እነኚህ ወንጌሉን በአገሩ ውስጥ በ1541 ዓ.ም. ስብከት ጀምረው ነበርና። ከዚያ በላይ ፖርቱጊዞችና ሆላንዶች ከጃፓን ጋር ስለነበራቸው መገበያየት ከስፓንያ ምንም ውድድር ለማየት አልወደዱም ነበር።
በ1601 የስፓንያ ታላቅ መርከብ ሳን ፍራንሲስኮ ከማኒላ ወደ ሜክሲኮ ሲሄድ መውጅ አጋጥሞት በጃፓን ጠረፍ ላይ በቶክዮ ዙሪያ በቺቦ ሲጠፋ መርከበኞቹ በኗሪዎች አማካይነት ድነው ስላምታ ይሰጡና የመርከቡ አለቃ ሮድሪጐ ደ ቪቨሮ ከሾጉን (ደጃዝማች) ቶኩጋዋ ኢኤያሱ ጋራ ተገናኙ።
በኅዳር 23 ቀን 1602 ዓ.ም. የስምምነት ውል ተፈራርመው፣ እስፓንያውያን በምሥራቅ ጃፓን ውስጥ አንድ ፋብሪካ ለመሥራት፣ የማዕድን ሠራተኞች ከ"አዲስ ስፓንያ" (ሜክሲኮ) ወደ አገሩ ለማስገባት፣ የስፓንያ መርከቦች አስፈላጊነት እንደሆነባቸው ጃፓንን ለመጎብኘት ተፈቅደው፣ ደግሞ የጃፓን ተልእኮ ወደ እስፓንያ ቤተ መንግሥት እንዲጓዝ ተወሰነ።
በቶክዮ ዙሪያ ይሰብክ የነበረው መነኩሴ ሉዊስ ሶተሎ ወደ አዲስ እስፓንያ (ሜክሲኮ) አምባሳደር ሆኖ እንዲላክ ሾጉኑን አስረዳቸው። በ1602 ሶተሎ ከተረፉት እስፓንያዊ መርከበኞችና ከ22 ጃፓናውያን ጋራ ለሾጉኑ በእንግሊዛዊው ዠብደኛ በዊሊያም አዳምስ በተሠራው መርከብ በሳን ብዌና ቨንቱራ ላይ ተሣፍሮ ወደ ሜክሲኮ ተጓዘ። አዲስ እስፓንያ ደርሶ እንደራሴውን ሉዊስ ደ ቨላዝኮ አገናኘ። እሳቸው ታዋቂውን ዠብደኛ ሰባስትያን ቪዝካይኖ አምባሳደር ሆኖ ወደ ጃፓን ለመላክ ተስማሙ። በተጨማሪ ከጃፓን ወደ ምሥራቅ እንደ ሆኑ የታሰቡትን "የወርቅና የብር ደሴቶች" እንዲፈልግ ልዩ የሆነ ትእዛዝ መደቡት።